የሰላም ሚኒስቴር ከሰራተኞች ጋር ውይይት አካሄደ
የሰላም ሚኒስቴር ከሰራተኞች ጋር ውይይት አካሄደ
ሐምሌ 23 ቀን 2016ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር በ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከሰራተኞች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን የከፈቱት የሰላም ሚኒስቴር የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መብራቱ ካሣ የዛሬው መድረክ በ2016 በጀት ዓመት ተቋማችን ያከናወናቸውን ተግባራት በጥልቀት በመመልከት የተገኙ መልካም ውጤቶችን ለማጠናከር እና ያጋጠሙ ችግሮችን ደግሞ በመፍታት በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ ሥራ ለመስራት ያለመ ነው ብለዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የሰላም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ አለሙ ዘወሌ የሰላም ሚኒስቴር በ2016 በጀት ዓመት በሰላም ግንባታ፣ በግጭት መከላከልና አፈታት፣ በብሔራዊ መግባባት፣ በፌደራሊዝም ሥርዓት ግንባታ፣ በመንግሥታት ግንኙነት ማጠናከር እና በአስተዳደራዊ ተግባራት የተሰሩ ዋና ዋና ተግባራትን እና የተከናወኑ ሀገራዊ የሰላም የንቅናቄ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል።
የ2017 በጀት ዕቅድ ያቀረቡት የሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አዱኛ በቀለ የዘንድሮ ዕቅድ በየደረጃው ካሉ አመራሮችና እና ሰራተኛች ሰፊ ውይይት ተደርጎበት የታቀደ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በጀት ዓመት የሚከናወኑ አንኳር ተግባራት ተለይተዋል ብለዋል። ያሉ ሀገራዊ ዕድሎች እና ስጋቶች በዕቅዱ ውስጥ በጥልቀት ታይተዋል ያሉት አቶ አዱኛ በያዝነው በጀት ዓመት ህዝብን በስፋት የሚያሳትፋ ትልልቅ አገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰላም የንቅናቄ ኮንፍረንሶችን ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል።
በቀረበው ሪፖርት እና ዕቅድ ከሰራተኞች አስተያየትና ጥያቄ ተነስቶ በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝም እና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ በክቡር አቶ ቸሩ ጌታ ገነነ ማጠቃለያ ተሰጥቶባቸዋል።
ክቡር አቶ ቸሩ ጌታ ገነነ በንግግራቸው ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን የተለያዩ ንቅናቄዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ለስኬታማነቱም የሁሉም አመራርና ሰራተኛ ቁርጠኝነትና ቅንጅት በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል።
የዘላቂ ሰላም ስራ ረጅም ጊዜ የሚወስድ እና የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት ክቡር አቶ ቸሩ ጌታ ገነነ ሁሉም ዜጋ ግጭትን ለመከላከል እና ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሰላም ባለቤት እንዲሆን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከስብሰባው ጎን ለጎን ሰራተኞች የደም ልገሳ አካሂደዋል።
በመጨረሻም በ2016 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች የእውቅና እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።