የሰላም ሚኒስቴር የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር አበረታች ስራ እየሰራ ነው - ቋሚ ኮሚቴው
የሰላም ሚኒስቴር የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር አበረታች ስራ እየሰራ ነው - ቋሚ ኮሚቴው
ሚያዝያ 20 /2017 ዓ.ም(ሰላም ሚኒስቴር )፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሰላም ሚኒስቴር የክልል መንግስታትን እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን አመላከተ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የፌዴራልና የክልል መንግስታትን እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሰራቸው በርካታ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ግብረ መልስ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ የአጋርና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር እየሰራ መሆኑንና ሀገራዊ አንድነትን እና አብሮነትን ለማጎልበት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራቱን እንደ መልካም አፈጻጸም አንስቶ እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስቧል።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን በመዘርጋት የተመደበለትን በጀት በአግባቡ መጠቀሙን በሪፖርቱ መመልከቱን ጠቁሟል።
በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ትኩረት እንዲሰጥ እና፣ ለግጭት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን አስቀድሞ በመለየት የግጭት ምንጮችን ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በትብብር የማጋለጥ ስራዎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ የአሰራር ስርዓቶቹን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሰራቸው ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ የቅድመ ግጭት ትንበያ ስራዎች በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሆነው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የግጭት መከታተያ ቴክኖሎጂው ለህብረተሰቡ በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆንና በዚህ ዙሪያ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች ተደጋጋሚ የሚዲያ ሽፋን የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችም አስገንዝበዋል።
የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ በበጀት አመቱ 25 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማወያየት አቅዶ ከ18 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማወያየት መቻሉን ተናግረዋል።
ሰላምን በዘላቂነት ለማምጣት ህብረተሰቡን ማወያየት ቀዳሚው ተግባር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ሁሉንም በሚያግባቡና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መስራት እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
ክቡር አቶ መሀመድ በየአካባቢው የሚከሰቱ ጥቃቅን ግጭቶችን የብሄርና የሃይማኖት መልክ ያለው በማስመሰል በተዛባ ግንዛቤ ግጭቱን ከማስፋፋት ይልቅ፣ የግጭቱን እውነተኛ መንስኤ መፈለግና መፍትሄ መስጠት የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሃይማኖት ተቋማት፣ከሌሎች ተቋማት እና ከከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
#የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት