የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ተመረቁ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) ብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለ13ኛ ዙር በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና የወሰዱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመረቁ፡፡

ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት የወጣቶችን የሀገርና ፍቅር የሚያሳድግ፣ ማኅበረሰባዊ ትስስርና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናከር፤ ለሀገር ግንባታ በጎ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ፕሮግራም መሆኑ ተገልጿል፡፡

“ፕሮግራሙ ወጣቱን በአመለካከትና በሥነ-ምግባር እንዲታነጽ ከማድረግ ባሻገር በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ፣ ሀገራቸውን እና ማኅበረሰባቸውን እንዲያውቁ የሚያደርግ እና የሀገር ፍቅር ስሜት በውስጣቸው እንዲሰርጽ የሚያደርግ ስለሆነ በተሰማሩበት ሁሉ ማኅበረሰብን በማገልገል መልካም አርአያ የሚሆኑበት ነው” ሲሉ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አበበ ወርቁ በምረቃ መርሐ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል፡፡

አቶ አበበ ሀገራዊ ፕሮግራሙ፡- የዘላቂ ሰላም እና የሀገር ግንባታ ሥራውን በአብሮነት፣ በወንድማማችነት እና በአንድነት ከዳር ለማድረስ ወጣቱን በስፋት ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ በማስገንዘብ ወጣቱ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እና መርሆችን ተቀብሎ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ብዝኃነት ጥሩ ዕድል መሆኑን ተረድቶ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት እና በሌሎችም ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ትልቅ አበርክቶ ያለው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል “እንደ ሀገር የሰላም እሳቤ በትውልዱ አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ እና ብሔራዊ መግባባት እንዲዳብር ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባር የበጎ ፈቃድ ሠልጣኞችን አሠልጥኖ ሥምሪት በመስጠት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዚህ በጎ ዓላማ ሀገራዊ ፕሮግራም አጋር በመሆኑ እና በሰላም ግንባታው አሻራ በማሳረፉ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል፡፡

ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ “ይህ ዕለት የሥልጠና ማጠናቀቂያ ቢሆንም ቀጣይ በተግባር የምትፈተኑበት የሥምሪት ጅማሬያችሁ በመሆኑ የሚጠብቃችሁን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በብቃትና በመልካም ሥነ ምግባር የምትወጡ የሰላም ልኡካን እና አምባሳደር እንድትሆኑ አደራ” በማለት ለተመራቂዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ “ሠልጣኝ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም በሥልጠናው ያገኛችሁትን ክህሎት በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ በትምህርት ዓለም ካገኛችሁት ዕውቀት እና መልካም ሥነ ምግባር ጋር በማጣመር ማኅበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት እንደምታገለግሉና የበጎነት ተምሳሌት እንደምትሆኑ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን” ሲሉም አክለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊና የከንቲባ ተወካይ አቶ ደስታ ደምበሌ በመርሐ ግብሩ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር “ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ወጣቱን ከተለያዩ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ጋር የሚያስተዋወቅ በመሆኑ የርስ በርስ መስተጋብሮቻችንን የሚያጠናክርና የመተጋገዝና የመደጋገፍና ባህላችን የሚያጎለብት ነው፤” በማለት ፕሮግራሙ ለሀገር ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት የጎላ ሚና እንዳለው አመላክተዋል፡፡