የማህበረሰብ ተኮር ምክክር በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የጋራ ትርክት ለመገንባት እንደሚያግዝ ተገለፀ
የማህበረሰብ ተኮር ምክክር በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የጋራ ትርክት ለመገንባት እንደሚያግዝ ተገለፀ
ሰኔ14/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) የሰላም ሚኒስቴር ከክልል ሰላምና ጸጥታ አካላት ጋር በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ማህበረሰብ ተኮር የምክክር ሂደት ዋና ዓላማ በየአካባቢውና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች በየደረጃው ስልጡን ምክክርን በማድረግ የጋራ አረዳድን እና ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም የማህበረሰብ ተኮር ምክክር ህብረተሰቡ የመፍትሄ አካል እና ችግር ፈቺ እንዲሆን ለማስቻል ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ተቋሙ የማህበረሰብ ተኮር ምክክርን ቁልፍ ተግባር በማድረግ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ተኮር ውይይት ማህበረሰቡ በአካባቢውና በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የጋራ ትርክት ለመገንባትና የውይይት ባህልን ለማዳበር ያግዛል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው በውይይት የሚገኙ ግብዓቶችን መነሻ በማድረግ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታትና ምርጥ ተሞክሮ የተገኘባቸውንም በማስፋት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም የማጽናት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በምክክር የተገኙ ልምድና ዕውቀትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ከየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ እስከ ታችኛው መዋቅር ቀበሌና መንደር ድረስ በማውረድ ማህበረሰቡ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የማህበረሰብ ተኮር ምክክር የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡