''ሀገራችን ፀንታ እንድትቆምና ፈተናወችን እንድታልፍ ካስቻሏት መካከል የከበሩና የዳበሩ ማህበራዊ ሀብቶቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ'' ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ
''ሀገራችን ፀንታ እንድትቆምና ፈተናወችን እንድታልፍ ካስቻሏት መካከል የከበሩና የዳበሩ ማህበራዊ ሀብቶቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ'' ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ
ሰኔ 18/2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር "ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችን " በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች እና የማህበራዊ የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፣ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንዲሁ የተገኘች ሀገር አይደለችም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈች ጠንካራ ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ሀገራችን ፀንታ እንድትቆምና ፈተናወችን እንድታልፍ ካስቻሏት መካከል የከበሩና የዳበሩ ማህበራዊ ሀብቶቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።
አክለውም በሀገራችን ከ72 በላይ የከበሩ ማህበራዊ ሃብቶቻችን አሉ ያሉ ሲሆን እነዚህ ሃብቶች በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ያላቸው፣ በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመሆናቸው ግጭቶች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ በመለየት እና ግጭቶችን የመከላከል ሚናቸው አይተኬ መሆኑን ገልፀዋል።

ጉምቱ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ባለበት ሀገር ትናንሽ ልዩነቶቻችን ሰፍተው ችግር ውስጥ ልንገባ አይገባም ያሉት ክቡር አቶ መሐመድ የዛሬው መድረክ በማህበራዊ ሃብቶቻችን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመለየት እና እነዚህን ሃብቶች ለሀገር ግንባታ እና ለብሔራዊ መግባባት ለማዋል መሆኑን ገልፀዋል።

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር መካከል በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እና በህብረተሰቡ መካከል የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና የንቅናቄ ስልቶችን ቀይሶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ሀገር በቀል ማህበራዊ ሃብቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ለሰላም ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት ለማዋል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ተስፋ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ናቸው ያሉ ሲሆን የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ህብረተሰቡን በማቀራረብና በማስታረቅ ድርሻቸው ትልቅ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ችግር የተምሳሌት ችግር ነው ያሉት ፕ/ር መስፍን ከአለፋት 40 እና 50 ዓመታት ወዲህ ተምሳሌት/አርያ/ የምናደርገው ሰው ማግኘት ከብዶናል ፤ ወደ ቀድሞው ማንነታችን ልንመለስ ይገባል ብለዋል።
"ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችን " በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች እና የማህበራዊ የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ እንደቀጠለ ነው።