የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሀገር አቀፍ አፈጻፀም ላይ የልምድ ልውውጥ ተደረገ
የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሀገር አቀፍ አፈጻፀም ላይ የልምድ ልውውጥ ተደረገ
ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፣ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሀገር አቀፍ አፈጻፀም ላይ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።
የሰላም ሚኒስቴር ከሐረሪ ሕዝብ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ያለፉት አምስት ዓመታት ሀገር አቀፍ ስኬታማ ክንውን ዕውቅና ሰጥቶ ቀጠይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
በመድረኩ ተገኝተው ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለብሔራዊ አንድነትና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ገንቢ አስተዋፅኦ እያበረከተ፣ ገዢ ትርክትን እየገነባ ያለ እና ሀገራችን ለጀመረችው የብልፅግና ጉዞ ስኬት በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አበርክቶ ያለው ፕሮግራም መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሐረሪ ሕዝብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ኦርዲን በድሪ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ብሔራዊ አንድነትን በማስቀጠል እና ማሕበራዊ ትስስርና መስተጋብር በማጠናከር የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያቃለለ ያለ ሀገራዊ ፕሮግራም መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም የወጣቶችን የሥራ ባህል በማጎልበት እና ሀገራዊ የሰላም እሴቶች በማጠናከር ብሔራዊ መግባባትን እውን እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በስፋት በማሳተፍ በክልሉ በተለይም በሰላም ግንባታው ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን በመቻሉ በክልሉ ሰላምን ለማስፈን የተሠሩ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ቶፊቅ መሐመድ አመላክተዋል፡፡
ፕሮግራሙ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት ማኅበራዊ መስተጋብሯ የጠነከረ ሀገር ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተመላክቷል።