በኦሮሚያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባሉ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ
በኦሮሚያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባሉ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ
ግንቦት 2/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከኦሮሚያ እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባሉ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት አካሂዷል ።
በውይይቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መኮንን ባይሳ ዞኑ የበርካታ ጀግኖች ባለቤት እና ለሰላምና ፀጥታ መከበር ዋጋ የከፈሉ አባት አርበኛች መፍለቂያ መሆኑን ገልፀው የኦሮሞን ማህበረሰብ በኪነ ጥበብ እና በባህል ከፍ ያደረገም ነው ብለዋል።
ዞኑ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሰላምና በፍቅር የሚኖርበት ነው ያሉ ሲሆን ህዝባችን ከፀጥታ አካላት ጋር እጅ እና ጓት ሆኖ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።

በውይይቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይሌ ጉርመሣ በበኩላቸው የዛሬው የውይይት ዓላማ ከዚህ በፊት በጋራ በዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር የገባነውን በመገምገም በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን ሰላምና ፀጥታ ከፍ ማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

''የመንግስታት ግንኙነት በኢትዮጵያ'' ሰነድ የሰላም ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኙነት ባለሙያ በሆኑ በአቶ ፀጋብርሃን ታደሰ የቀረበ ሲሆን የኦሮሚያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሪፖርት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ የግጭት መከላከልና አፈታት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ታመኔ ሳህሉ በኩል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ውይይቱን ያጠቃለሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሣ በቀጣይ በጋራ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እና የፅንፈኛ አስተሳሰቦችን ለመዋጋት በትብብር ሥራዎችን እናከናውናለን ብለዋል።