የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰልጣኝ ብሔራዊ የሰላም በጎፈቃደኞች ለተማሪዎች ድጋፍ አደረጉ
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰልጣኝ ብሔራዊ የሰላም በጎፈቃደኞች ለተማሪዎች ድጋፍ አደረጉ
ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየሰለጠኑ የሚገኙ የ14ኛ ዙር ብሔራዊ የሰላም በጎፈቃደኛ ወጣቶች በጅማ ከተማ ለሚገኘው የድል ፍሬ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።
ሰልጣኝ የሰላም አምባሳደሮቹ ድጋፉን ያደረጉት በስልጠናው ጊዜ ከሚቀርብላቸው ምግብ ቀንሰው ባሰባሰቡት 121 ሺህ ብር ለት/ቤቱ ተማሪዎች ምገባ አገልግሎት እንዲውል ያበረከቱት መሆኑ ተገልጿል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኢንጅነር ኤፍሬም ዋቅጅራ የሰላም አምባሳደሮቹ ለድል ፍሬ ት/ቤት ያደረጉት ድጋፍ ሰው ካለው ነገር ለሌሎች ሲያካፍል የሚገኘውን ውስጣዊ እርካታና ደስታ በውል መገንዘባቸውን በተግባር ያሳየ ድጋፍ መሆኑን ገልፀዋል።
የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አሸናፊ አዱኛ በበኩላቸው በጎ ፈቃደኞቹ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ለጅማ የድል ፍሬ ት/ቤት ያደረጉት ድጋፍ ወደፊት በሚሰማሩበት ቦታ የላቀ የበጎነት ተግባራትን በማከናወን ሕዝብና ሀገርን ለማገልገል ያላቸውን ዝግጁነት ያሳዩበት አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።
የድል ፍሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሙሉነህ ታደሰ ሰልጣኝ ወጣቶቹ ለተማሪዎቻቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሰላም ለኢትዮጵያ!