የሰላም ግንባታ
የሰላም ግንባታ
የሰላም ግንባታ የሰነ-ልቦና፣ የሰብዕና እና የሰው ሁለንተናዊ ዕድገት ግንባታ ተብሎ ሊወሰድም ይችላል፡፡
የሰላም ግንባታ ሰብዓዊ ሀብት ግንባታ፤ የአመለካከት፣ የክህሎት፣ የአስተሳሰብ፣ የተግባቦት ክህሎትን፣ የፈጠራ ችሎታን፣ ትምህርትና የሁለንተናዊ ክህሎት ግንባታ ተብሎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ በጣም ቀለል ባለ አነጋገር የሰላም ግንባታ ማለት የተግባቦት ወይም የግንኙነት ግንባታ ማለት ነው።
በሌላ መልኩ ተጋጭተው፣ ተለያይተው፣ ተራርቀው፣ ተፈናቅለው፣ ተጐድተው፣ ዳግም ላለመገናኘት ተማምለው፤ በነፍስ የሚፈላለጉ ግለሰቦች/ቡድኖች ውይም ማኅበረሰቦች ግንኑነቶቻቸውን መልሰው መገንባት፤ ማስታረቅ፣ ማወሃድ፣ ማዋደድ፣ ማደስ፤ እንደገና ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ እና ሕይወትን እንደገና የመጀመር ሂደት የሰላም ግንባታ ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡
የሰላም ግንባታ አብዛኛውን ጊዜ ከግጭት፤ ከነውጥ፤ ከአመጽ፤ ከጦርነት በኋላ፣ የሚከወን ድርጊት ቢሆንም ከጦርነቱ ወይም ከግጭቱ ጎን ለጎን የሚካሄድ ተግባርም ነው፡፡
የሰላም ግንባታ፣ የሀገር ግንባታ፣ የዜጐች ግንባታ፣ የሀገራዊ ማንነት፤ የብሔራዊ ስሜት፤ የሀገር ወዳድነት፤ የሀገር ፍቅር ግንባታ ተብሎ ሊጠቀስም ይችላል፡፡ ሲጠቃለል የሰላም ግንባታ የአዲስ አስተሳሰብ፣ የአመራር ብቃት እና የክህሎት ግንባታ ተብሎ ሊገለፅ ይችላል፡፡
የሰላም ሚኒሰቴር የሰላም ግንባታ ስራዎችን ለማጠናከርና አወንታዊ ሰላም ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና ለማሳደግ፤ግለሰብ፣ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሰላም ግንባታ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን በስፋት በማሳተፍ እና በባለቤትት መንፈስ እንዲሰሩ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን፣ አሰራሮችን እና ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!