ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ለሰላም
ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ለሰላም
ግጭት በሰው ልጆች የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚያጋጥምና ከሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ ማንነት ጋር የሚቆራኝ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህን ተፈጥሮአዊ የሆነውን ግጭት የከፋ ጉዳት ከማድረሱ እና ውድመት ከማስከተሉ በፊት መቆጣጠር ደግሞ አንዱ የሰው ልጆች የቤት ሥራ ነው፡፡
የሚፈጠሩ ግጭቶችን ቀድሞ ለመፍታት ከሚያገለግሉ መንገዶች ውስጥ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው።እንደ ሀገር በማህበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት የዳበሩና የተከማቹ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አሉን፡፡
ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማቱ ለመቻቻል፣ ለእኩልነት፣ ለመልካም አሥተዳደር መስፈን እና ለፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በመፍታት ሰላም እንዲፈጠር ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ያላቸው፣ በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመኾናቸው በተገልጋዮች ዘንድ የሚታመኑ ናቸው፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ በመለየት እና ግጭቶችን የመከላከል ሚናቸው የጎላ ነው። በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልኾነባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላምን በማስፈን እና ፍትሕን በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።
በየአካባቢው የሚሰየሙ ጉምቱ ሽማግሌዎች፣አባገዳዎች፣የጎሳ መሪዎች መረጃዎችን መሠረት አድርገው ሰላምን ሊያመጣ በሚችል ሁኔታ የእርቅ ሥነ ሥርዓቱን ይፈጽማሉ። ሽማግሌዎቹ የእድሜ ባለፀጋ በመኾናቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ከሕግ ይልቅ የሕሊና እና ማኅበራዊ ኀላፊነትን በመጠቀም ሁለቱን አካላት ወደ ሰላም መንገድ ያመጣሉ።
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር መካከል በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እና በህብረተሰቡ መካከል የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና ንቅናቄ ስልቶችን ቀይሶ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ሲሆን ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ለሰላም ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት ለማዋል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!