ሰላምን ለማፅናት የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚና በሚል ርዕስ ውይይት እየተካሄደ ነው
ሰላምን ለማፅናት የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚና በሚል ርዕስ ውይይት እየተካሄደ ነው
ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ሰላምን ለማፅናት የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚና በሚል ርዕስ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ በሀገራችን በህግ ተመዝግበውና ዕውቅና ተሰጥቷቸው ከሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ሀገራዊ ሰላምን ለማምጣት እና በአንፀራዊነት እየመጡ ያሉ የሰላም ሁኔታዎችን ለማጽናት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚጠበቅባቸው ሚና ላይ የጋራ መግባባት ለመድረስ እና በቀጣይ በሀገራችን ይካሄዳሉ ተብለው ለሚጠበቁ ወሳኝ የፖለቲካ ሁነቶች አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዲሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሰላም ማለት ልማትን፣ ነጻነትን፣ ፍትሕንና ደስታን ያለ ማንም ዕንቅፋትነት ለማግኘት መቻል ነው ብለዋል።
ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሁለት ዓይነት ማኅበረሰብ ይፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ያዳበረ ሕዝብ እና ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ያዳበሩ ልሂቃን፤ እኛም እንደ ፖለቲካ ልሂቅ አንድም የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ባህል መገንባት፤ አሊያም ለኢትዮጵያውያን ባህልና ዕሴት የሚስማማ ዴሞክራሲን በጋራ መቀመር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴር ሁለንተናዊ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አግባብነት ካላቸውን አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የዛሬው መድረክም የዚህ አንድ አካል ነው ብለዋል።
ከህብረተሰቡ ጋር በተሰራው ሰፊ የውይይት ሥራ እና የህግ ማስከበር ሥራ አሁን በሀገራችን አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ያሉት ክቡር አቶ መሐመድ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የፖለቲካ ፖርቲዎች በተናጠል ያላቸውን ዓላማ የሚያሳኩት ዘላቂ ሰላምና የተረጋጋች ሀገር ሲኖር ነው ያሉት ደግሞ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ናቸው። አክለውም ቀጣይ የሚደደረገው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ '' ሰላምን ለማፅናት የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚና'' የሚል ሰነድ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ደዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።