"ኢትዮጵያ ትናንት በሠራችው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ችግሮችን ተቋቁማ አዳዲስ ታሪኮችን እየሠራች ያለች ሀገር ነች።" ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ
"ኢትዮጵያ ትናንት በሠራችው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ችግሮችን ተቋቁማ አዳዲስ ታሪኮችን እየሠራች ያለች ሀገር ነች።" ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ
ሐምሌ 20/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፣ በማዕከለዊ ኢትዮጵያ ክልል በምሥራቅ ጉራጌ ዞን በመስቃንና በማረቆ ልዩ ወረዳ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ ልማት እና የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ የተገኙ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ ፕሮጀክትን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ በኢፌዴሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን በመግለፅ ሀገርን አልምቶ ፣ አሳድጎና አበልፅጎ ለትውልድ ለማስረከብ ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች የሚጠቀስ መሆኑን አመላክተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለው ኢትዮጵያ ትናንት በሠራችው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ብዙ ችግሮችን ተቋቁማ አዳዲስ ታሪኮችን እየሠራች ያለች ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።

የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን "በዞናችን የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ከመትከል ባሻገር አብሮነትን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጠናክር እንዲሁም መንግሥት ለሰው ተኮር ልማት ያለውን ትኩረት የሚያሳይ ነው"፤ ብለዋል።
በምሥራቅ ጉራጌ ዞን የምሥራቅ መስቃን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መሐመድ ሰብራላ (ዶ/ር) በበኩላቸው "በወረዳችን የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ ልማት እና የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ለሕዝባችን ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው" ፤ ብለዋል።

በመርሀ ግብሩ የሰላም ሚኒስቴር፣የሀገር መከላከያ ሚኒስቴርና የፍትህ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች የተሳለፉ ሲሆን የችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያካተተ ሲሆን ፤ የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ መንከባከብ እና የተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል አመራሩና ሕዝቡ በቅንጅና በአብሮነት መሥራት እንዳለባቸው ተገልጿል።