የሃይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ሰላም ሚኒስቴር
የሃይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ሰላም ሚኒስቴር
የሃይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
አራተኛው ሀገር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰላም ኮንፍረንስ የ2ኛ ቀን መርሃ ግብር በሐረር ከተማ ኢመም አህመድ ስታዲየም እየተካሄደ ነው።
በኮንፍረንሱ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽዎ እያበረከቱ ይገኛሉ።
የሃይማኖት ተቋማቱ በዘርፉ እየተወጡ ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረው በተለይም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት የሁሉም ሚና መጠናከር አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሰላምን ለማስፈንና አፅንቶ ለማዝለቅ የጀመረውን የሰላም ጉባኤ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ነው ያሉት።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እንዳሉት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው ሰላምን አብዝተው ሊሰብኩ ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመነጋገርና በመመካከር በመፍታት ሰላምን ማፅናት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
በተለይም ለሰላም፣ ለአብሮነት እና ለአንድነት መጠናከር በጋራ በመቆም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት ጉባኤው አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚረዱ በርካታ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ችግሮች እንዲፈቱ አድርጓል።
በዚህም የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ መከባበር፣ ሰላም፣ አብሮነት እና ይቅርታን የሚያጎለብቱ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ሰላምን በማስፈን በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ጠቁመው የሀገራችን ሰላም እንዲጸና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ያቀርባል ብለዋል።

በሐረር ከተማ በሚገኘው ኢማም አህመድ ስታድየም በተዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሃይማኖት ተቋማትና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።