የሰላም ሚኒስቴር “ሰላማችንን ማፅናት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በየደረጃው ከሚገኙ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል
የሰላም ሚኒስቴር “ሰላማችንን ማፅናት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በየደረጃው ከሚገኙ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል
ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር “ሰላማችንን ማፅናት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ለዘላቂ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በየደረጃው ከሚገኙ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

በውይይቱ ላይ “ሰላምን ማፅናት ለሀገራዊ ማንሰራራት” የሚል ሰነድ በሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ እና “የሀገራችንን ሰላም ለማፅናት የተሰሩ የፀጥታ ስራዎች፣ የተገኙ ውጤቶች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች” የሚል ሰነድ በፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በኩል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የአንዳችን ሰላም ለሌላችን ሰላም፣ የአንዳችን ህመም ለሌላችን ህመም በመሆኑ በጋራ መስራት፣ መናበብ እና መቀናጀት ያስፈልጋል ያሉት ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ ክልሎች ከአጎራባች ክልሎች ጋር የጋራ የፀጥታ ፎረም በማቋቋም እየሰሩት ያለውን ሥራ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር “ሰላማችንን ማፅናት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በቀጣይ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ሰፋፊ ውይይቶችን ያካሂዳል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ተቋማችን በክልሎች ያለውን የሰላምና የግጭት ሁኔታዎች በፍጥነትና በጥራት የምንከታተልበት “የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ “ ስርዓት እየገነባን እንገኛለን ብለዋል፡፡
አንድ ቀበሌ ላይ የተፈፀመ ወንጀል በወንጀል አይን ብቻ ነው ማየት የሚያስፈልገው ያሉት ክቡር አቶ መሀመድ ነገሩን በማስፋት የብሔር መልክ ማሲያዝ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ አክለውም ያለውን አንፃራዊ ሰላም ይበልጥ የሚያሰራ እንጅ የሚያዘናጋ ሊሆን አይገባም ያሉት ሲሆን ሰላማችንን በተጨባጭ የሚያሳዩ የኮሙኒኬሽን ሥራዎችም በተከታተይ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ ሀገራችንን ለማፍረስ ያልተሞከረ አጀንዳ የለም ያሉ ሲሆን ይሁን እንጅ መንግስት ሥራዎችን በጥበብ በመስራቱ፣ ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት እና አመራር በመገንባቱ እና በችግር ውስጥ ሆኖ ሰላምን የሚፈልግ ህዝብ በመኖሩ ሀገር የማፍረስ አጀንዳው ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም የሚከፈለውን ዋጋ በመክፈል ማፅናት እንደሚያስፈል የገለፁ ኮሚሽነሩ ሀገራችን ለብቻዋ ተገንጥላ የምትቀመጥ ሀገር ባለመሆኗ የራስን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ዲፕሎማሲ ግንኙነትም እየተገነባ ይገኛል ብለዋል፡፡